Saturday, April 20, 2013

ለስራ ፈላጊ/ ማስታወቂያ


ለካ ሃዘን ሲበረክት የስራ እድልም ይፈጥራል
በየማስታወቂያ ሰሌዳው
          ከንፈር መጣጭ ይፈልጋል”
                  የሚል ጽሁፍ ተለጥፏል፡፡
@           @          @

ሌባና ፖሊስ


አንደኛው…..
         ድምጹን ከፍ አድርጎ ወደ አንዱ አቅጣጫ ጣቱን ንደቀሰረ 
                                      ሌባ ሌባ ሌባ…………… ያዙልኝ ይለናል፤
                                                   ፖሊስ ይመስለናል፤
ሌባ የተባለው ጣት የተቀሰረበት ታምቡር በሚበጥስ ሰማይ ጠቀስ ድምጹ
                          ወደ አመልካቹ እያመለከተ ሌባ ነው ያዙልኝ…
                          እንዳያመልጣችሁ እያለ ይለምናል፤
                                                         ግራ ተግባተናል፤
ሁሉም ባንድ አቅጣጫ
                        ባንድ አይነት እሩጫ
 ጣቱን ተቀሳስሮ እርስ በርስ ሲባረር
                                       ሲወቃቀስ ስናይ
                                          ሌባና ፖሊሱን በየት በኩል እንለይ፡፡          
@           @          @

Saturday, February 16, 2013

እንባዬን በዋንጫ......


በጉንጮቼ ወለል ላይ ከተረፈረፉት ዘለላዎች መሀል
………………………………………………………..አንዲቷን በጥሼ
የናፍቆቴን መጠን የብዛቱን ነገር ቀምሜ ጠንስሼ
የውስጤን ቃጠሎ የመጨስ መንደዴን በላዩ ከልሼ
……………………………………………………ይኸው ሰድጃለሁ
…………………………………………………..ይድረስህ ብያለሁ
እንባዬን በዋንጫ ሞልቼ ልኬያለሁ፡፡
አለበት በውስጡ መሻቴ ጠረንህን
አይንህን መራቤ መፈለጌ አንተን፡፡
በድምጽህ እርቀት አይሆኑ የሆነው
በመጥፋትህ ሰበብ ልቤ የቆሰለው
የኔ ያልኩት ልብህ ነውና የጨከነው
የሆንኩትን ሁሉ ሆነህ እንድታየው
እንደደራሽ ሆኖ በፈረስ ጉልበቱ ልብህን እንዲንጠው
ንዴቴን የያዘ አንኳር እንባም አለው፤
ግን አንተ ውዴ ሆይ ዋንጫውን ከሞላው
በብዛት በመጠን ልቆ የሚልቀው
ላንተ ያለኝ መውደድ ሀያሉ ፍቅሬ ነው፡፡

Saturday, January 12, 2013

የዚያን ሰሞን


አሁን አሁን አይኖችህ ሸሽተወኝ
ቀኔም ጠቁሮ ጨልሞብኝ
ጀንበር ጠልቃ መሻሽቶብኝ
ሆንኩኝ እንጂ ግራ የገባኝ
ያኔ ድሮ የዚያን ሰሞን
የማይ ጊዜ አይኖችህን
በብርሃንህ የፈካሁኝ
ያንተ ድምቀት ያደመቀኝ
በደስታህ ደስታ ያለኝ
ከሴት ሁሉ ተመርጬ
      አለም በጄ የሆነልኝ
ፍቅር በዝቶ የተረፈኝ
ነበርኩልህ የሞላልኝ
             የዚያን ሰሞን ወረት ይዞህ
አፍክተኸኝ በፈገግታህ
አጥግበኸኝ በቁልምጫህ
አሙቀኸኝ በዳበሳህ
አሁን አሁን ስትሸሸኝ
ሆንኩኝ እንጂ ቆሌ የራቀኝ
የዚያን ሰሞን የኔ እያለህ
አይ ነበረ በውስጥ አይንህ
የኔ አለም አንተ እንደሆንክ
ሳትቀር በፊት ወረት ይዞህ
@           @          @

እቴ ሜቴ…


እ ቴ ሜቴ የሎሚ ሽታ
ያ ሰውዬ ምናለሽ ማታ
 @       @      @
ሆድ ይሉት ባላንጣ ጠላት ተፈጥሮብሽ
ውስጥሽ እያነባ ላይሽን አሳምረሽ
በማይስቀው ጥርስሽ ስታገጪ ቢያይሽ
አገሬው….
መች ከፋት እያለ ተጠቋቆመብሽ
አንቺም…..
ከሳት አይኑ ለመደበቅ የጨለማ ንግስት ሆነሽ
በበልቶ ማደርና በሰው መሆን ክብር ወፍራም ገመድ
             ዳርና ዳር ተጠፍንገሽ
             ግራና ቀኝ እየተናጥሽ
መወለድሽን እየረገምሽ እናትሽን ስትወቅሺያት
የራስሽን ገላ እየተጸየፍሽ ደካማ ነው ስትዪ ሴትነት
መለስ አድርገሽ ደግሞ ሴትነትሽን ስትመርቂ
የተሰደሩ ጡቶችሽን ዳሌሽን ስታደንቂ
የህልውናሽን ጠበቃ ማዕድሽን ሚሞላውን
                      እራትሽን ሚያዘጋጀውን
ሴት መሆን መሆኑን ለአፍታ ስታውቂ
አንዴ ስታለቅሺ አንድዜ ስትስቂ
                እቆምሽበት ቦታ
ሴት አዳሪ ሚልሽ ሊያድርሽ እየመጣ
እቴ ጓደኛዬ እቴ የሎሚ ሽታ
ያ ትልቅ ሰውዬ ምን አለሽ ግን ማታ
     @       @     @

ሴት...


ያዩኛል….
ከሞዴል ሊገዳደር አልተገነባም ሰውነቴ
ከአለም ቆነጃጅት ተፋልሜ ዘውድ አልደደፋሁም በአናቴ
……………………………………..ግን ያዩኛል
የቀልባቸውን እኔ ላይ ማረፍ ምስጢር ይጠይቁኛል
   እና እኔም እላቸዋለሁ….
ሞገሴ የተንሰራፋው በጭስ የደከመ አይኔ ላይ ነው
ትክ ብላችሁ ብታነቡት ቀለሙ ራሮት ነው
የአዘኔታ ማጨጃ ሰፊ ማሳ ይህ አይኔ ነው
ፀሀይ ወጥታ የምትጠልቀው እዚሁ አይኔ ላይ ነው
እነሆኝ እንግዲህ ምስጢሬ ይሔው ነው
                    እላቸዋለሁ
እልና ደግሞ…… የለም እላላሁ……የለም
…………..ይህ ብቻማ አይደለም
የአዳምን ህልም የፃፍኩበት መዳፌ ላይ ነው ምስጢሬ
በአፍ በአፉ ያጎረስኩት ቁራሼ ነው ምስክሬ
እንደ ከንአን ምድር ማርና ወተት የሚያዘንቡት
መንታ ጡቶቼ ላይ ነው ውበቴን ያተምኩት
በአብራኬ ክፋዮች ሽንት ነው
                   ታሪኬን ጀርባዬ ላይ የሳልኩት
በፀጉሬ ጉንጉን ነው ጎተራዬን የሰራሁት
                   እላቸዋለሁ…..
እልና ደግሞ…… የለም እላለሁ……የለም
ይህ ብቻማ አይደለም………………
ታሪኬን ታሪካችሁን በሚተርከው እርምጃዬ ነው ቀልባችሁን የገዛሁት
ሀዘኔና ሀዘናችሁን በጻፍኩበት ገጼ ላይ ነው ልባችሁን የማረኩት
                                        እላቸዋለሁ………
ለቀንቶ መራመዳችሁ እኮ የኔ መጉበጥ ተከፍሏል
ለወዛችሁ መንጨፍጨፍ ላቤ በግንባሬ ላይ ወርዷል
ለሰውነታችሁ መደልደል አጥንቴ ተግጧል
ለፈገግታችሁ ድምቀት ጥርሶቼ ረግፈዋል
አረማመዴም ታዲያ ይሄንኑ ያትታል
                         እላቸዋለሁ……..
እልና ደግሞ……የለም እላለሁ……የለም
ይህ ብቻማ አይደለም………
ከመንገዳችሁ እያስቀረ የሚገትራችሁ ከበራፌ
እልፍ ትርጉም ውስጡ ያለው …..
                        ምስጢሩ ነው ሴትነቴ…
    @        @         @