Sunday, December 9, 2012

በቃልህ እቀፈኝ


አንዳንዴ……..
    የሚወዱትን ሰው ንግግር ሲሰሙ
እንደ ጠዋት ጸሃይ……
ለሰስ ባለው እጇ ገላን ስትዳስስ
የቆፈንን እስር እንደምትበጣጥስ
እንደ እናት ፈገግታ
             ገና ከሩቅ ሲያዩት
የመከራን ድራሽ እንደሚያጠፉበት
እንደ አባት ምቹ ክንድ …….
ከህይወት ውጣ ውረድ እንደሚያመልጡበት
…………………አንዳንዴ
       የወደዱትን ሰው ንግግር ሲሰሙ
በፈርጣማ ክንድ ውስጥ ገብቶ እንደማረፍ
ከሰፊ ደረት ላይ ወድቆ እንደመንሳፈፍ
ምቾትን ይሰጣል ልክ እንደመታቀፍ፡፡
              አንዳንዴ……….
@           @          @


   Hold me

When ever you spoke to me
     When ever I hear your voice
I got courage to face the dark
    Your words are like a warm big hug.


Saturday, December 1, 2012

ምን ነበር


ምን ነበር ከቀን ቀድመው ቢሮጡ
አመት ጎትተው ቢያመጡ
ዛሬን እየዘለሉ ነገ ላይ ቢቀመጡ
     ምን ነበር ላንዳንዴ እጅ ከዘመን ቢረዝም
     የአመታት ቀመር ልኬት በአንድ እርምጃ ቢወሰን
     ነገ ላይ ያለውን ለማቅረብ ዛሬን ማለፍ ባይኖርብን
ምን ነበር………..
        @         @         @

ውድ


ትበላው ትጠጣው ሁሉ ውድነቱ እያስመረረህ
ከእጅ ወደአፍ ቅንጦት ሆኖ እጅና አፍህ ተኳርፈውህ
እንኳ ለመዘነጫ
…………….እንኳንስ እኔን ልትጨምር
           መኖር በራሱ ተወዶብህ
እንደዚህ ስትቸገር ስትባዝን እያየሁህ
አትጨነቅ ወዳጄ ቅያሜ ‘ንኳ አይገባኝም
ከተወደዱት ተወድጄ ውዴ በለኝ አይወጣኝም፡፡

    @           @          @

ለጣውንቴ


ባሌ……………………………………
በእንቅልፍ በወለምታው ያንቺን ስም ሲያነሳ
አንቺ ጋር የበላውን እኔ ላይ ሲያገሳ
በደግዬው ባልሽ ህመሜን ባልረሳ
እንዳወዳደቄስ ዛሬም አልነሳB


Saturday, November 24, 2012

ደሊላ


 


ግዳይ እረፍርፈህ ምድረ ያዳምን ዘር

ወንድነትህ ታፍሮ ኒሻን ስትደረድር

ተዘናግተህ እንዳይሆን ጀግና ሲልህ አገር

(ግዴለም ተጠንቀቅ ስትደርስ ከኔ አጥር)

…………………..ምክንያት…………………………

የሶምሶምን እራስ መላጨት ያስቻለ

የጭኖቼ ሙቀት ዛሬም ከኔ አለ።

Monday, November 19, 2012

ገጣሚ አይደለሁም...


ገጣሚ አይደለሁም……..
የሼክስፒር ብዕር
የገብርዬ ቀለም
ለኔ አልተሰጠኝም
ቃላት እንደውሀ
ቅኔ እንደ ጅረት
ካንደበቴ አይፈስም፣
ግን እንደው ላንድ ቀን
የግጥም ምች መቶኝ
ወይ ገጣሚ ቡዳ መንገዴ ላይ በልቶኝ
ለመጻፍ ብሞክር ያውም ስለ ፍቅር
የመጀመሪያው ግጥሜ ስላንተ ይሆን ነበር
ከዛ እጽፋለሁ… እንዲ እያልኩ ጽፋለሁ……….
………………………..አይንህ……………………..
አይንህ እንደ ሰማይ... እንደ ጸደይ ሰማይ
..................ኮልሎ የጠራ ነው
የቀረ ህይወቴን ምእራፍ በምእራፍ፣ ገጽ በገጽ ሆኖ
አይንህ ላይ ተጽፎ፣ ተጽፎ አነባለሁ
ያን የጠራ አይንህን ትክ ብዬ ሳየው
እንዲ እያልኩ እጽፋለሁ
አይንህን አያለሁ፣አይንህ ወዳለሁ
እንቅልፍ ባይረታብኝ ቀን ሙሉ አይቼህ
.......ባድር መች ደክማለሁ
ግን ገጣሚ አይደለሁም…
የሼክስፒር ብዕር
የጸጋዬ  ቀለም
ለኔ አልተሰጠኝም
ቃላት እንደውሀ
ቅኔ እንደ ጅረት
ካንደበቴ አይፈስም፣
ግን እንደው ላንድ ቀን
በተኮላተፈ ሸፋፋ አማርኛ
ለመጻፍ ብሞክር
ያውም ስለ ፍቅር
የመጀመሪያው ግጥሜ ስላንተ ይሆን ነበር
ከዛ እጽፋለሁ……እንዲ እያልኩ እጽፋለሁ
ከንፈርህ ወይን ነው…….
ከንፈርክን ወዳለሁ
እንኳን ስሜህ ብቻ…..
እንደ ድፎ ዳቦ…
እንደ እማዬ እንጎቻ
ገምጬ ብውጥህ መቼ ጠግብሀለሁ
ከንፈርህን ወዳለሁ…. ከንፈርህ ማር አለው
የተራበች ነፍሴ ጠግባ የምታድረው
አምራ የምትደምቀው
ከከንፈርህ ወለላ የበላሁ እንደሁ ነው
ብዬ እጽፍላሁ…..
ከዛም እጽፋለሁ እንዲ እያልኩ ገጥማለሁ
የልብህ አታሞ የልቤ ድለቃ
ከቤትሆቨን ቅኝት ከተራቀቀው ስልት
ለጆሮዬ የሚጥም ይፈጥራል ሙዚቃ
ምታት ያለው ጣትህ የጀርባዬን ክርክር
በስልት በመላ አርጎ እንደ ክራር ሲያከር
ገላዬ ይዘፍናል በማላውቀው ቋንቋ
ይመታል አስክስታ
የጎጃም እንቅጥቅጥ የጎንደር ድለቃ
እንዲ ደሞ እላለሁ
ደረትህ ሰፊ ነው
ደረትህን ወዳለሁ
የቀን እንግልቴን
የዕለቱን ድካሜን
እንኳን ተኝቼበት
ገና ደረትህ ሳየው እረሳለሁ
ደረትህን አያለሁ………ደረትህ ሰፊ  ነው
ደረትህን ወዳለሁ
እንኳን ባንድ ሌሊት
በድሜዬ ርዝመት
ዝንት አለም ብጨፍር ብገላበጥበት
የማያልቅ ሜዳ ነው…………ደረትህ ሰፊ ነው
ደረትህን ወዳለሁ
ግን ገጣሚ አይደለሁም…………………………………..
የሼክስፒር ብዕር
የጸጋዬ ቀለም ለኔ አልተሰጠኝም
ቃላት እንደውሃ
ቅኔ እንደ ጅረት ካንደበቴ አይፈስም
ግን እንደው ላንድ ቀን
የግጥም አማልክት ዘይት ቀብተውኝ
የቅኔዋ አድባር ደጇን  ብትከፍትልኝ
ከዛ እኔ ደፍሬ ለመጻፍ ብሞክር
ያውም ስለ ፍቅር
የመጀመሪያው ግጥሜ ስላንተ ይሆን ነበር
ከዛ እንዲ እላለሁ
ደረቴን ነፍቼ ላ’ለም አወራለሁ
እሱ እላለሁ………….እሱ ግጥሜ ነው
እኔ ደግሞ ግጣሙ……………………ገጣሚው

ድልድይ


ፈገግታዬን ቀምተኸኝ
        እንደዳመንኩ ቀርቻለሁ
ባፈረስከው ቤቴ ተሰብሬ
         መንታ መንታውን አንብቻለሁ
ግና… ድንገት ትመለስ እንደው
      መንገድህ እንዳይታጎል
            አዳፋ እንዳይነካው መረገጫህ
ጸአዳነትህን አቆሽሾ
          በእድፈቱ እንዳያጎድፍህ
………… ይኸው
ከእንባዬ ኩሬ በላይ
        ትልቅ ድልድይ ሰራሁልህ፡፡

@           @          @

አፉ በለኝ.....


እውነት ነው ከእቅፍህ ተንሸርትቼ ከደረቱ ወድቄያሁ
ከንፈሮችህ ቢነጥፉብኝ ከንፈሮቹን ጠብቼያለሁ
ጠረንህ ቢሰነፍጠኝ መአዛውን መርጬያለሁ
ቆፈንህን ለማራገፍ ከሙቀቱ ሰምጬያለሁ
ቢሆንስ ታዲያ ምናለ ፍቅር እንደው ይታገሳል
ሰባት መቶ ሰባ ሰባት ሰባት ሺ'ም ይቅር ይላል
እናም………………………………………
የሱ ጣዕም ከከንፈሬ ከገላዬ ባየለቀኝም
ስለተወኝ መጥቼያለሁ አፉ በለኝ አይለምደኝም።

ሚስጥር ለወንዶች...

ሴት ልጅ አንዴ አፍቅራህ ልቧን ብትሰጥህም
ከከንፈር ቀለሟ አታስበልጥህም...

ሚስጥር ለሴቶች...

ወንድ ልጅ በፍቅርሽ  ተረቶ ቢወድቅም
 ከ'ንግሊዝ እግር ኳስ አትበልጪበትም

እጀ እጅ......

.........አንተ
        ይቅርብኝ እያልኩህ ነካካኸኝና
እሱ.......
        አልፈልግም አለኝ እጅ እጅ አልኩትና...